Covid 19 Information

ኮሮና ና የህዳር በሽታ
ቻይና ዉሃን ግዛት ውስጥ ሰዎች እየሞቱ ነው በሽታው የዱር አራዊት ሥጋ በተመገቡ ሰዎች ነው የጀመረው እየተባለ በመገናኛ ብዙሃን መዘገብ ከተጀመረ ከድሴምበር (ታህሳስ) ወር መጀመሪያ ጀምሮ ቀናት ሳምንታትና ወራት አለፉ የአለርት ሆስፒታልም ይህን ዜና ሰምቶ ሁሉም የስሞኑ መወያያ አድርጎታል
በአሜሪካ ፕሬዚደንቱን ጨምሮ የቻይና በሽታ እያሉ አሹፈዋል በዛን ሰሞን አሜሪካ ውስጥ እንደ ሲዲሲ ዘገባ በጉንፋን 1 መቶ ሰማኒያ ሺ ሰው ሆስፒታል ገብቶ ነበር 10ሺ ሞተዋል የበሽታ መቆጣጠሪያ ባለስልጣናቱ ይህ በየአመቱ የጉንፋን ወቅት ተለመደ ነው በማለት ችላ ብለው ነበር
በጥቅምት ወር የጀመረው ይህ ኮቪድ አስራ ዘጠኝ( covid 19) የተባለ በሽታ ሁሉንም ታላላቅ አገራት አዳርሶ ህዝብ እየጨረስ በመጋቢት ወር መጀመሪያ ማርች 13 2020 አዲስ አበባ መግባቱ በምርመራ ተረጋገጠ ስጋት አገሪቱን አስጨንቆ ያዛት ይህ የሆነው የህዳር በሽታ አገራችን ገብቶ ብዙ ህዝብ ከፈጀ በመቶ አንድ አመቱ ነው ከዛን ጊዜ ጀምሮ ህዳር12 ቀን በብዙ የአገራችን ክፍሎች ሰው ከየደጁ ቆሻሻ ሰብስቦ ማቃጠል የተለመደ ነው
አለርት ሆስፒታል ዝግጅቱን የጀመረው ቀደም ብሎ ቢሆንም የመጀመሪያው ታማሚ እንደታወቀ ፈጣን አርምጃ መውሰድ ጀመረ ለቅድመ ምርመራ የሚሆን ቦታ ተዘጋጀ ለማቆያና ለማከሚያ ሊሆኑ የሚችሉ ቦታዎችንም መምረጡ ደግሞ ቀጣይ ስራ ነበር በአገሪቱ የነበረው መደናገጥ በሆስፒታሉም ታይቶ ነበር ሌላ ቦታ እንደታየው ሁሉ ሳይታመሙ የታመሙ ሳያረጁ ያረጁ ሳይወልዱ የሚያጠቡ ሳይሰበሩ የተሰበሩ ነበሩ ስንቱ ጀግና እንዳይሆን ሆነ ? በዚህ ወቅት በዚህ አስፈሪ ጊዜ ነበር ካለምንም ግዴታና ጥቅማጥቅም ጥቂት የሆሰፒታሉ የቁርጥ ቀን ልጆች ብቅ ያሉት “ እኛ እያለን ኮሮና አይስፋፋም”!! እነዚህን የሆስፒታሉ ታሪክ ሲያስታውሳቸው ይኖራል
ከመቶ አመት በፊት ስፓኒሽ ፍሉ ተብሎ የሚጠራው አለም አቀፍ ወረርሺኝ በተከሰተ ጊዜ በአለም ላይ (500፣000፣000) አምስት መቶ ሚሊዮን ህዝብ የነዋሪዎቹ (ሢሦ )አንድ ሶስተኛ ታሞ ነበር (50፣000፣000 )ሃምሳ ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል የመጀመሪያ ምልክት የታየው አሜሪካ ውስጥ በጃንዋሪ 1918 እ.ኤ.አ. ነበር ሁለት ወራት ቆይቶ ከማርች 4-11 ካንሳስ አሜሪካ አንድ መቶ ወታደሮች በካምፕ ውስጥ ይህ ኢንፍሉዌንዛ እንደያዛቸው ተረጋገጠ ቫይረሱ ኤችዋን ኤንዋን (H1N1) ተብሎ ተጠራ በአሜሪካ 675 000 ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺ ሰው ገድሎአል ወደ አውሮፓ ሲገባ ፈረንሳይን እንግሊዝን እስፔይንን ይዞ ሌሎችን እያጠቃ ወደ እሲያና አፍሪካ ተዛምቶ የመላው አለም ወረርሺኝ ሆነ
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ብዙ ወረርሺኞች እንደነበሩ ቢታወቁም የተመዘገቡት ጥቂት ብቻ ናቸው በ1698 ሉዶልፍ በላቲን አማርኛ መዝገበ ቃላቱ ጉንፋንን ( catarrh ) ሲል አስፍሮታል 1706 በዓጼ እያሱ አንደኛ ፣በ1747 በዓጼ እያሱ 2ኛ፣እንዲሁም1835-36 በትንሹ ራሰ ኣሊ ዘመን ፣በ1839 ኣድዋ ለይ እንዲሁምከሃያ ሺ በላይ ወታደሮች የሞቱበት ብዙ ህዝብ ያለቀበት በ1889-1891 በታላቁ የረሃብ ጊዜ (ዓጼ ሚኒሊከ ስልጣን እንደያዙ) ከፍተኛ ወረርሺኞች ነበሩ ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ በሌላው አለም 1803፣ 1833፣1837 1847 ከተከሰቱት ጋር ወቅታቸው ይገጣጠማል
እ.ኤ.አ.በ1918 አንደኛው የኣለም ጦርነት እንዳለቀ የእስፓኒሽ ፍሉ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በኤደን ባህረ ሰላጤ በኩል በባቡር ተሳፍሮ እንደሆነ ይነገራል የህዳር በሽታ ሃምሳ ሺ(50፣000) ስው ገድሎ ሲያልፍ አስር ሺ የሚሆኑት ከአዲስ አበባ ነበር ከነበሩት 8 የጤና ባለሙያዎች 4ቱ በመሞታቸው አንድ የሃይማኖት ሰው” አምላክ በመጀመሪያ የጤና ባለሙያዎችን ቀጥሎ ህዝቡን ወሰደ” ብለው ተናግረዋል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን (ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ) በበሽታ ከተያዙት መካከል አንዱ ነበሩ በወቅቱ የዛሬ 101 አመት በህዳር 11 ቀን 1911ዓ/ም የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ዳይሬክተር በኃላም የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር የነበሩት ብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደስላሴ ለህዝቡ በዘመኑ ሊደረግ የሚገባውን የጥንቃቄ ማስታወቂያ አውጥተው ነበር ህዝቡም በዘመኑ ባለው እውቀትና ግንዛቤ በሽታውን ታግሎታል
ከእስፓኒሽ ፍሉ (የህዳር በሽታ )በኃላም ብዙ ወረርሺኞች ነበሩ 1957 ኤሺያን ፍሉ፣1968 ሆንግ ኮንግ ኢንፍሉዌንዛ እና ሌሎች ይጠቀሳሉ
የአየር ንብረት ለውጥ፣የከተሞች ህዝብ ብዛትና ተጨናንቆ መኖር፣የህዝብ ፈጣን እንቅስቃሴ የአገራት አለመረጋጋት፣ የህዝብ መፈናቀልና ስደት ምክኒያት”በቅርቡ ታላቅ አለምኣቀፍ ወረርሺኝ ተከስቶ ሳንዘጋጅ እንዳይይዘን ከስፓኒሽ ፍሉ (የህዳር በሽታ )መቶ አመታት በኃላ ተዘጋጅተናል ወይ?” በሚል ያየህይራድ ቅጣውና ሚርጌሳ ካባ የተባሉ ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ስጋታችውን (Ethiopian journal of public health vol 32 no1 2018 GC) ገልጸው ነበር በአሁኑ ሰኣት እስከ ኦገሰት 26 2020 እ.ኤ .አ. ድረስ በኣለም ላይ ከሃያ አራት ሚሊዮን በላይ በአገራችን ከአርባ ሶስት ሺ በላይ ህዝብ ተጠቅቶአል ያጣነውም የሰው ህይወት ብዙ ነው በህዳር በሽታ ዘመን ከ1918 -1920ድረስ በሽታው ተዛምቶ ቆይቶ ነበር ክትባት እስካልተገኘ ድረስ አሁንም ለአመታት ሊቆይ ስለሚችል ሁላችንም ጥንቃቄ በማድረግ ጉዳቱን መቀነስ ይጠበቅብናል ለዚህም አምላክ ይርዳን

ዶክተር ይሄይስ ፈለቀ
በእለርት ማእክል ሜዲካል ዳይሬክተር
ነሃሴ 2012 ( august 2020)